አሳዛኝ ታሪክ ከአማኑኤል ሆስፒታል በዶ/ር ዮናስ ላቀው

ADVERTISMENT

አሳዛኝ ታሪክ ከአማኑኤል ሆስፒታል

በዶ/ር ዮናስ ላቀው

‘ራውንድ’ እያደረግን ነው። አዲስ የገቡ ሶስት ታካሚዎች አሉ። ሁለቱን ካናገርኩ በኃላ የሶስተኛው ተራ ሲደርስ ሲስተር ‘መምጣት አይችልም’ አለችኝ። ያለበት ላየው ሄድኩኝ። ጉልበቶቹ ታጥፈው ይንፏቀቃል፤ መራመድ አይችልም። እግሮቹ ሰልለዋል። ስለህመሙና ስለህክምናው ተነጋገርን። ለምን መራመድ እንደማይችል ግን ሊነግረኝ አልፈለገም። ለተጨማሪ መረጃ እናቱን ማናገር ጀመርኩኝ።

ሁለት ወንድ ልጆች እንደነበሯቸውና አንደኛው ልጃቸውና ባለቤታቸው ከብዙ ጊዜ በፊት እንዳረፉ ነገሩኝ። ብቸኛ ልጃቸው ህመም የጀመረው ከአምት አመት በፊት እንደነበረና የተለያዩ የባህል ህክምና እንደሞከሩለት ነገሩኝ። ነገር ግን ብዙ ለውጥ እንዳልነበረውና ህመም መሆኑን ባለማወቃቸው ወደ ህክምና እንዳልወሰዱት ነገሩኝ። ይጠፋብኛል ብለው ሰግተው ቤት ውስጥ ለአራት አመታት አስረው እንዳስቀመጡትና በዚያ ምክኒያት መራመድ እንደማይችል ሲናገሩ አይናቸው እንባ አቀረረ። ከአንድ አመት በፊት ሰዎች ‘ለምን ህክምና አትወስጂውም?’ ብለውኝ ነበር። እኔም ለመውሰድ አስቤ ነበር። ነገር ግን በአቅራቢያችን የአእምሮ ህክምና የለም። እዚህ ለመምጣት ደግሞ አቅም የለኝም። አሁን ራሱ የመጣነው ጎረቤት ገንዘብ ሰብስቦልን ነው። አሉ።

‘የሚታከም መሆኑን ባውቅ ኖሮ ልጄን እንዲህ አላደርግውም ነበር።’ አሉ። እንባቸው መውረድ ጀመረ። በእናት አንጀት የሚሰማቸውን ሀዘንና ፀፀት ሳስበው ውስጤ ተረበሸ። ሶፍት ከኪሴ አውጥቼ አቀበልኳቸው።

ያን ቀን ከስራ ሰወጣ የአእምሮ ህመም ግንዛቤ የተስፋፋ ቢሆን፣ ተደራሽና ጥራት ያለው አገልግሎት ቢኖር የልጃቸው ሁኔታ እንዴት የተለየ ሊሆን እንደሚችል እያሰብኩ ነበር።

የአእምሮ ህክምና ግንዛቤን መፍጠር የሁላችንም ሀላፊነት ነው።

መልካም ቀን!