አዴፓ የቱ ነው ? አምባቸው ወይንስ ዮሃንስ ቧያለው? | ሬሞንድ ኃይሉ

ADVERTISMENT

ከቀናት በፊት የአማራ ክልል ርዕሥ መስተዳድርን ቃለ-መጠይቅ ተመልክቼ ያለኝን አድናቆት ገልጬ ነበር፡፡ አምባቸው መኮንን(ዶ/ር) ስለ ሰላም ደጋገመው መስበካቸውም ይበል የሚያስኝ መሆኑን አወድሻለሁ፡፡ ይህ ወዳሴዬ ግን ትናንት በሌላ ሀሳብ ተሞግቷል፡፡ ዋልታ ቴሌቪዥን ላይ እንግዳ ሆነው የቀረቡትን የአዴፓ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዮሃንስ ቧያለው አስተያየቶች ስሰማ ግራ ተጋብቻለሁ፡፡ በድርጅቱ የስልጣን ተዋረድ ውስጥ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት እነዚህ አመራሮች የሚያወሩት ነገር ለየቅል ነው፡፡
.
አምባቸው ወደራሳቸው ደጋግመው የሚመለከቱ ዮሃንስ ነገሮቹን ሁሉ ውጫዊ የሚያደርጉ ሰው ሆነው አግኝቻቸዋለሁ፡፡ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበርና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሆኑትን አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የሚመሩት ህዝብ የሰላም እጦት ያለበት መሆኑን አምነው ይህን ለመፍታት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የመንግስት ዋና ተግባር የህዝብን ሰላምና ደኅነነት ማስጠብቅ መሆኑንም በመገልፅ ለዚህ ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ የአማራ ክልል ርዕሥ መስተዳድር በስልጣን ዘመኔ ላሳካ የምፈልገው ዋና ጉዳይም ሰላማዊ የሆነ ክልልን መፍጠር ነው ብለዋል፡፡
.
ይህ የእሳቸው ሀሳብ ክልሉ በተወሳሰበ የሰላም እጦት ውስጥ እንዳለ የሚያረጋግጥና እሱን ለመፍታትም አመራሩ ቁርጠኛ መሆኑን የሚያሳይ ይመስላል፡፡ የአማራ ክልል ርዕሥ መስተዳደርና የአዴፓ ሁለተኛ ሰው አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)ነገሮችን ወደ ውጭ ከመግፋት ይልቅ ችግሮቹን ለመፈታት ቁርጠኛ እንደሆኑ ቢያረጋግጡም በድርጅቱ ተዋረድ የእሳቸው ተከታይ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ቧያለው ግን የሚያወሩት ነገር ሌላ ነው ፡፡
.
የአዴፓ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ትናንት ምሽት ከዋልታ ቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ አማራ ክልል ከሌላው የሀገሪቱ ክፍል የተለየ የሰላም ችግር የለበትም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አቶ ዮሃንስን የእሳቸው ፓርቲ የሚመራውን ክልል ሰላም ማጣት እኔ አልነግራቸውም፡፡ በእርግጥም ምዕራብ ጎንደር ላይ የተደራጁ ሽፍቶች እንደ ሊቢያ አማፅያን ሰው አግተው ገንዘብ እንደሚደራደሩ፣ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ያሉ አመራሮችን ከቢሮ አባሮ የጎበዝ አለቃን መሾም መለመዱን፣ ሀገር ሊፈርስ ነው በሚል የተሳሳተ ወሬ የአማራ ገበሬ በሬውን እየሸጠ የጦር መሳሪያ ሲገዛ መዋሉን፤ እኔ ለእሳቸው በጭራሽ አላስረዳቸውም፡፡ ከዛ ይልቅ ዶ/ር አምባቸውን በስልጣን ዘመኔ ማሳካት የምፈልገው ነገር የክልሉን ሰላም መመለስ ነው ለምን እንዳሉ ብቻ ይጠይቋቸው፡፡
.
አቶ ዮሃንስ በመሳሪያ የታገዘ የከተማ ላይ ግጭትን የሚያስተናግድ ብቸኛ ክልል ይዘው ከሌላው የተለየ ስጋት የለብንም ማለታቸው ሳያንስ አክራሪ አክቲቪስቶች አማራን አይወክሉም በማለት ብሄር ሰጭና ነፋጊ ሆነዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደ ሀገር የአማራ ፖለቲካ እንደ ክልል ፅንፈኞች ያሉበት መሆኑ የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህ እውነት አቶ ዮሃንስ አመኑም አላመኑም ያለና የሚኖር ነው፡፡ መፍትሄውም አክራሪ ብሄርተኝነት ለምን በዚህ ደረጃ የፖለቲካ ምህዳሩን ሊቆጣጠር ቻለ? ምን ቢደረግስ ሊከስም ይችላል? የሚለው ላይ መስማማት እንጅ ማንነትን መስጠትና መንፈግ አይደለም ፡፡
.
የአዴፓ ፅህፈት ቤት ኃላፊው ፅንፈኛ ብሄርተኞች አማራ አይደሉም ማለታቸው ሳያንስ የክልሉን ህዝብ የሚወክሉ በርካታ ፓርቲዎች አሉ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ክልሉ እኔ የማላውቀው የራሱ ምርጫ ቦርድ ከሌለው በስተቀር የአማራን ህዝብ የሚወክሉ ፓርቲዎች ቁጥር ጥቂት እንደሆነ አያከራክርም፡፡ እኔ በጋዜጠኛው ቦታ ብሆን አቶ ዮሃንስ “አማራን የሚወክሉ ብዙ ፓርቲዎች አሉ” ሲሉ እባክዎት ስማቸውን ቢያስታውሱን ማለቴ አይቀርም ነበር፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴን በቅርቡ የተቀላቀሉት ሰው ሰለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ የሰጡት ምላሽም ፈገግ የሚያሰኝ ነው፡፡
.
በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ ድርጅትዎ ያለው አቋም ምንድነው ? የተባሉት አቶ ዮሃንስ፡፡ ያው እንደሌሎች የሚል ገራሚ መልስ ሰጥተዋል፡፡ እንደ ሌሎች ማለት ምን ማለት ነው? ከ30 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚያስተዳድር ፓርቲ የክልሉን ነዋሪ መብት የሚያስጠብቀው እንደሌሎች እየሆነ ነው? እንደሌሎች ማለተስ በራሱ ምንድን ነው? አዲስ የተመሰረተው ኢዜማ የተሰኘው ፓርቲ ምርጫው በቀጣይ መካሄድ የለበትም የሚል አቋም ይዟል፡፡ ህወሓትና አብንና ኦነግ የመሰሉ የብሄር ድርጅቶች በአንፃሩ ቀጣይ ዓመት ምርጫውን ማካሄድ ለድርድር አይቀርብም እያሉ ነው፡፡ የአቶ ዮሃንስ ሌሎችን እንመስላለን ሀሳብ ሚዛኑ የቱ ጋር ነው?
.
የአዴፓ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የቋንቋ አጠቃቀም ያስደንግጣል፡፡ አንድን ክልል የሚመራ ፓርቲ ኃላፊ መሆናቸውን የዘነጉባቸው ንግግሮች ብዙ ናቸው፡፡ ስለአማራ ገዥ መደብ ሲያብራሩ ተፈፀሙ የሚባሉ የታሪክ ጠባሳዎችን ሲያወሱ የአዴፓ መድረክ ላይ የተገኙ እንጅ ሌላው ኢትዮጵያዊ እየሰማቸው እንደሆነ የተረዱ አይመስሉም፡፡ 
.
ፖለቲከኝነታቸውን ታሳቢ ያላደረጉ ግለሰባዊ የቋንቋ አጠቃቀሞቻቸው ብዙ ናቸው፡፡ ፖለቲካ የቃላት ጨዋታ ነው፡፡ በቃል የሚነሳ በቃል የሚተው ብዙ ነው፡፡ አቶ ዮሃንስ ግን ይህን ዘንግተዋል፡፡ ደስ ሲላቸው ትንንሽ ታሪክ የሚያነሱ ሰዎች ሲሉ ይደመጣሉ፣ ሌላ ጊዜ እኛ የማንም “ገረድ” አይደለንም ይላሉ፡፡ 
.
“ገረድነት” እኮ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ድህነታችን የፈጠረው ነገር እንጅ ሰው ፈልጎት የሚሆነው ነገር አይደለም፡፡“ እንደ ፖለቲከኛ ዜጎች ከዚህ ህይወት የሚወጡበትን መንገድ መዘየድ እንጅ “ግርድናን ” ስድብ ማደረግ ተገቢ አይደለም፡፡ አቶ ዮሃንስ በነበራቸው ቆይታ እሳቸው ያሉበት አዴፓ የተሻለ የትናንቱ አድርባይ ስለመሆኑ ደጋግመው ነግረውናል፡፡ ፓርቲያቸውና የክልሉ መንግስት እየገጠመው ያለውን ችግር ከማቃለላቸውም በላይ መነሻውን በሙሉ ውጫዊ ሴራ ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ ይህ አቋማቸው ባለፈው ዕሁድ በክልሉ ቴሌቪዥን ቃለ-መጠይቅ ሲሰጡ ፓርቲያቸውን መንግስታቸውን ቆም ብለው ለመመልከት ከሞከሩት ዶ/ር አምባቸው ጋር ለየቅል የሚባል ነው፡፡ ጥያቄውም እሱ ነው፡፡ አዴፓ የቱ ነው? አምባቸው ወይንስ ዮሃንስ ቧያለው?