ከለገሃር ፕሮጀክት ለሚነሱ ነዋሪዎች ለመንግሥት ሠራተኞች የተገነቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሊሰጧቸው ነው

ADVERTISMENT

ከለገሃር ፕሮጀክት ለሚነሱ ነዋሪዎች ለመንግሥት ሠራተኞች የተገነቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች ሊሰጧቸው ነው

26 May 2019ውድነህ ዘነበ

ኤግል ሂልስ ለገሃር አካባቢ ከሚገነባው መለስተኛ የከተማ ፕሮጀክት ሳይት ለሚነሱ ነዋሪዎች፣ ቀደም ሲል ለመንግሥት ሠራተኞች በኪራይ ለመስጠት የተገነቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በጊዜያዊነት ሊሰጧቸው ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ፣ አዲስ አበባን በከፍተኛ ደረጃ ይለውጣል ለተባለው ግዙፍ ፕሮጀክት ከሰጠው 36 ሔክታር መሬት ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ለማንሳት የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ ነው፡፡

በዚህ ቦታ ላይ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንና በቀበሌ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ነዋሪዎች፣ ለመንግሥት ሠራተኞች በኪራይ ለመስጠት በተገነቡት ኮንዶሚኒየም ቤቶች በጊዜያዊነት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ሠራተኞች የተገነቡት ኮንዶሚኒየም ቤቶች በአራት ኪሎና በገላን አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡

የእነዚህ ቤቶች ብዛት 1,718 ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግንባታቸው መጠናቀቁ ተመልክቷል፡፡ ቤቶቹን ለመከራየት የአስተዳደሩ ሠራተኞች ቅጽ ሞልተው እየተጠባቁ ቢሆንም፣ አስተዳደሩ ግዙፉን ፕሮጀክት ለማስጀመር በጊዜያዊነት ለልማት የሚነሱ ነዋሪዎችን ለማቆየት ወስኗል ተብሏል፡፡

ለኪራይ የተገነቡት ቤቶች በአጠቃላይ በ45 ብሎኮች የሚገኙ ሲሆን፣ እያንዳንዳቸው በአማካይ ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ብር ወጥቶባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ለእነዚህ ቤቶች ግንባታ 365 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጓል፡፡ ከፍታቸው ባለአምስት ወለል የሆኑት ቤቶች ሙሉ ወጪያቸው የተሸፈነው ከአስተዳደሩ ግምጃ ቤት በተገኘ ገንዘብ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን፣ በአጠቃላይ 20 ሺሕ ቤቶችን ለመንግሥት ሠራተኞች ገንብቶ የማከራየት ዕቅድ ነበረው፡፡ ነገር ግን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመኑ አራተኛ ዓመት ላይ የሚገኝ ቢሆንም፣ ግንባታቸው የተጠናቀቀው 1,718 ቤቶች ብቻ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የቤቶቹ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ከመጠናቀቁም በላይ የመሠረተ ልማት የተሟላላቸው ቤቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡

ከለገሃር ፕሮጀክት ሳይት ለሚነሱ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች እንዲሁ ልደታ አካባቢ የመነገጃ ቦታ ለመስጠት መታሰቡም ታውቋል፡፡

ከአምስት እስከ ሰባት ዓመት ይፈጃል የተባለው የለገሃር የግንባታ ፕሮጀክት፣ ከ20 ዓመታት በላይ የዘመናዊ ግንባታ ልምድ ባለው የአቡዳቢ ግዙፍ ኩባንያ ኤግል ሂልስ የሚካሄድ ነው፡፡

ፕሮጀክቱን ለማስጀመር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር 10 ቀን 2011 ዓ.ም. የመሠረት ድንጋይ አኑረዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ከአራት ሺሕ በላይ አፓርታማዎች፣ ሦስት ሆቴሎችን ጨምሮ አንድ መለስተኛ ከተማ ሊኖሩት የሚገቡ በሙሉ እንደሚኖሩት በወቅቱ ተገልጿል፡፡

ከአካባቢው የሚነሱ ነዋሪዎች ግንባታው ሲጠናቀቅ ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው በመመለስ፣ ኑሮአቸውን በአዲስና በዘመናዊ መንገድ ይቀጥላሉ ተብሏል፡፡